SURAFEL
10 min readMar 6, 2021
  • የአስተዳደር ህግ እና ህገ መንግስታዊ መርሆዎች
    የአስተዳደር ህግ እና የህገ መንግስት ትስስር እና ተዛምዶ
    የአስተዳደር ህግ ጽንስቱ ሆነ ውልደቱ ከህገ መንግስት እንደመሆኑ ከዚህ የህግ ክፍል ጋር ብዙ ባህርያትን ይጋራል። ሁለቱም የመንግስትና የግለሰብ ግንኙነትን በሚመራው ‘የህዝብ አስተዳደር ህግ’ ተብሎ በሚጠራው የህግ ክፍል ውስጥ ይመደባሉ። አብዛኛዎቹ የአስተዳደር ህግ ጥያቄዎች በቀጥታ ሆነ በተዘዋዋሪ የህገ መንግስታዊነት ጥያቄዎችን ያስነሳሉ። የአስተዳደር ህግን በጥልቀት ለመረዳት ከተፈለገ ሂደቱ መጀመር ያለበት ህገ መንግስትን በማጥናት ነው። በምሁራኑ አንደበት ይኸው እውነታ እንዲህ ይገለፃል።
    የአስተዳደር ህግ ከህገ መንግስታዊ መሰረቱ ተለይቶ በደንብ ሊታወቅ ሆነ ሊጠና አይችልም።
    የአስተዳደር ህግ በህገ መንግስት ማስፈጸሚያ መሳሪያነቱ የዝምድናቸውን ገጽታ በሚገባ ለማወቅ ይረዳናል። በዚህ የተግባሪነት ሚናው በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት ላይ የተቀመጡትን የህገ መንግስታዊነትና የመንግስት አስተዳደር መርሆዎች እንዲሁም የግለሰቦች ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች በተጨባጭ እንዲረጋገጡ በማድረግ ህገ መንግስቱን በማስፈጸም ረገድ እንደ አንድ መሳሪያ ያገለግላል።
    እ.ኤ.አ በ1959 ዓ.ም. የጀርመን የፌደራል አስተዳደር ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት እንደተናገሩት የአስተዳደር ህግ ‘ተጨባጭ ህገ መንግስት’ ማለትም በተግባር የሚታይ ህገ መንግስት ነው።a የአንድ አገር ህገ መንግስት በዋነኛነት የዜጐችን ሰብአዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ፖለቲካዊ መብቶችና ነጻነቶች ይደነግጋል። የዜጐች መብት በሌላ ግለሰብ፣ ማህበር ወይም የንግድ ድርጅት ሊጣስ ይችላል። ትልቁ አደጋ ያለው ግን ከመንግስት በተለይም ከስራ አስፈፃሚው አካል በኩል ነው። መብቶች በሚገባ እንዲጠበቁ የመንግስት አስተዳደር ልኩ ተለይቶ በታወቀ የስልጣን ገደብ ውስጥ ሊከናወን ይገባል። ሆኖም ስልጣን ሁልጊዜ በህጉ መሰረት ግልጋሎት ላይ ይውላል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው። ስለሆነም የግድ በአግባቡ ሊገራና ልጓም ሊበጅለት ይገባል።
    የአስተዳደር ህግ የስልጣን መቆጣጠሪያ መሳሪያ ነው። ውጤታማ የስልጣን ቁጥጥር የዜጐች ህገ መንግስታዊ መብትና ነፃነት እንዳይጣስ ዋስትና ይሰጣል። መንግስቱን በተግባር እንዲተረጐም የሚደርገውም በዚህ መንገድ ነው፤ ስልጣንን በመቆጣጠር የዜጐችን መብት በተጨባጭ ማቀዳጀት።
    ይህ ሚናውን በሌሎች ህገ መንግስታዊ መርሆዎች አንጻርም ጎልቶ ይታያል። የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት በዋነኛነት ከሚደነግጋቸው የመንግስት አስተዳደር መርሆዎች መካከል ግልፅነት፣ ተጠያቂነትና የህዝብ ተሳትፎ ይገኙበታል።b ግልጽነት እውን የሚሆነው የመንግስት ባለስልጣናትና የአስተዳደር መስሪያ ቤቶች ለዜጐች መረጃ የመስጠት ግዴታቸው ከነዝርዝር አፈፃፀሙ ጭምር በህግ ተደንግጐ ሲገኝ ነው። ተጠያቂነት፤ ጠያቂውና ተጠያቂው ተለይቶ የተጠያቂነት ስልቱ በዝርዝር ህግ ካልተቀመጠ በተግባር አይረጋገጥም። የህዝብ ተሳትፎ እንዲሁ የአስተዳደር መስሪያ ቤቶች በሚሰጡት ውሳኔ በተለይም ደንብና መመሪያ ሲያወጡ በጉዳዩ ጥቅም ካላቸው ወገኖች ሀሳብና አስተያየት እንዲቀበሉ የሚያስገድድ የህግ ድንጋጌ ከሌለ የህዝብ ተሳትፎ በተጨባጭ አይታይም።
    ግልፅነትን፣ ተጠያቂነትንና የህዝብ ተሳትፎን በተግባር ለማረጋገጥ የሚወጡ ህጐች በአስተዳደር ህግ የሚካተቱ ናቸው። ይህም ማለት ህጉ እነዚህ የመልካም አስተዳደር መርሆዎች በተግባር እንዲረጋገጡ በማድረግ ህገ መንግስቱን ያስፈጽማል።
    በህገ መንግስትና በአስተዳደር ህግ መካከል ያለው የጠበቀ ግንኙነት ልዩነታቸው የላላ መሆኑን ያሳያል። ሊጠቀስ የሚችል ቀጭን ልዩነት ቢኖር የወሰን እና የህጎች የተፈጻሚነት ደረጃ (Hierarchy of Laws) ልዩነት ነው።
    ከወሰን አንፃር ህገ መንግስት አጠቃላዩን የመንግስት አወቃቀርና የሶስቱን የመንግስት አካላት ብሎም በፌደራልና በክልል መንግስታት ያለውን የስልጣን ክፍፍል ስለሚወስን በይዘቱ በጣም ሰፊ ነው። በአንፃሩ የአስተዳደር ህግ የአንደኛውን የመንግስት አካል ማለትም የስራ አስፈፃሚውን ስልጣን፣ ግዴታና ተግባር ብሎም የተግባራቱን ህጋዊነት የሚመለከት ህግ ነው። በህግ አውጭው የሚወጣ ህግ እና ፍ/ቤቶች የሚሰጡት ውሳኔ ህገ መንግስታዊነት ከጥናት አድማሱ በላይ ነው። ስለሆነም ከወሰናቸው አንጻር ህገ መንግስት መስፋቱ የአስተዳደር ህግ መጥበቡ እንደ አንድ የልዩነት ነጥብ ተደርጐ ሊወሰድ ይችላል።
    ሁለተኛው ልዩነት የህጎች መሰላል (Hierarchy of Laws) ሲሆን በህጐች መካከል ያለውን የደረጃ ዝምድና ይመለከታል። ህገ መንግስት የአንድ አገር የበላይ ህግ እንደመሆኑ ከህገ መንግስቱ ጋር የሚቃረኑ አዋጆች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎችና የአሰራር ልምዶች ዋጋ የላቸውም። የአስተዳደር ህግ በደረጃው ከህገ መንግስት ዝቅ ብሎ የሚገኝ እንደመሆኑ መቼም ቢሆን ከህገ መንግስቱ ጋር መጣጣም አለበት። ግጭት በተነሳ ጊዜ የበላይ የሆነው ህገ መንግስት ተፈፃሚነት አለው።
    የህግ የበላይነት
    ብዙ ምሁራን በየፊናቸው በምርምርና ጥናት ባገኙት እውቀት ተመርኩዘው የህግ የበላይነት መርህ ምንነት፤ ይዘትና ፋይዳውን አስመልክቶ አያሌ ንድፈ ሀሳባዊ ትንታኔዎችን አቅርበዋል። በአገራችን ደግሞ አባቶችና እናቶች በልባቸው ከተጻፈው እውነትና ከልምድ ከቀዱት ቱባ እውቀት በመነሳት የህግ የበላይነትን ጽንስ ሀሳብ በአንድ አባባል እንዲህ ይገልጹታል።
    “በፍርድ ከሄደች በቅሎዬ ያለፍርድ የሄደች ዶሮዬ!”
    የዚህ ተረትና ምሳሌ አንኳር መልዕክት ለጥቂት ሰዎች ብቻ የተገለጠ ሳይሆን በመላው ማህበረሰብ ዘልቆ የገባ ሀቅ ነው። እናም ይህን የህግ የበላይነት ፅንሰ ሓሳብ ጠንቅቆ ያወቀው ማህበረሰብ ህግ ሲጣስ፤ ፍትህ ሲጓደል፤ መብት ሲታፈን፤ ስርዓት አልበኝነት ሲነግስ፤ ማን አለብኝነትና በዘፈቀደኝነት ሲንሰራፋ፤ የግሉ የሆነችው ዶሮ ከህግ እና ከፍርድ ውጭ ሲቀማ ድምፁን አጉልቶ ይጮሀል፤ በህግ አምላክ! ይላል። የጮኸው የዶሮዋ ዋጋ አንገብግቦት አይደለም። የተወሰደችበት መንገድ እንጂ። በፍርድ ከሆነ፤ በህጉ መሰረት ከሆነ እንኳንስ ለዶሮ ለበቅሎም ቄብ አይሰጠውም።
    በህዝብ አስተዳደር፤ ፖለቲካ ሳይንስ፤ ህግ እና በሌሎችም የጥናት መስኮች የሚገኙ ምሁራን ስለ የህግ የበላይነት ምንነትና ይዘት ያላቸው ግንዛቤና አስተሳሰብ የተራራቀ ከመሆኑ የተነሳ ጽንሰ ሀሳቡ አሁንም ድረስ ቁርጥ ያለ ትርጓሜ አልተገኘለትም። አንድ የመስኩ ምሁር ይህንን ሀሳብ በማጠናከር እንዳብራራው፤
    ‘[T]he rule of law’, like ‘democracy’, has no single meaning: it is not a legal rule, but a moral principle, which means different things to different people according to their particular moral positions.c
    በዚህ የተነሳ በተለያዩ አገራት የፖለቲካና የህገ መንግስት ስርዓት ውስጥ ይዘቱና አፈጻጸሙ የተለያየ አንዳንዴ የማይጣጣም መልክ በመያዙ መሰረታዊ እሳቤው ወጥነት ርቆታል።
    ለምሳሌ በእንግሊዝ አንደኛውና የህግ የበላይነት መገለጫ በመንግስትና በግለሰብ መካከል የሚነሱ ክርክሮች በመደበኛ ፍ/ቤቶች ብቻ መዳኘታቸው ነው። ያ ማለት በእንግሊዛዊ አይን ፈረንሳይ ውስጥ የህግ የበላይነት የለም እንደ ማለት ነው። ምክንያቱም በፈረንሳይ በግለሰብና በመንግስት መካከል የሚነሱ ክርክሮች ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ድረስ የሚዳኙት ከመደበኛ ፍ/ቤት ትይዩ ራሱን ችሎ በተቋቋመ የአስተዳደር ፍ/ቤት ስርዓት አማካይነት ነው። በእንግሊዝ ሌላኛው የህግ የበላይነት ትርጉም የግለሰቦች መብትና ነፃነት መደበኛ ፍ/ቤቶች በቀረቡላቸው ተጨባጭ ጉዳዮች የሚሰጡት ውሳኔ ውጤት ነው የሚል ይዘት አለው። ይህ አስተሳሰብ በእንግሊዝ እውነት ቢሆንም የኛን አገር ጨምሮ የተጻፈ ህገ መንግስት ባላቸው እንደ አሜሪካ ባሉ አገራት የዜጐች መብቶችና ነፃነቶች በህገ መንግስቱ ላይ በጽሑፍ ይዘረዘራል።
    ከዚህ በተጨማሪ በሊብራል ዲሞክራሲ ስርዓት ውስጥ የህግ የበላይነት ማለት በህጉ መሰረት ከመግዛትና ከማስተዳደር ባለፈ የህጉ ይዘት (ለምሳሌ ፍትሐዊነቱ፤ የዜጐችን መብት ማክበሩ፣ ህጉ የወጣው ህዝብ ወዶና ፈቅዶ በመረጣቸው ተወካዮች መሆኑ ወዘተ…) ብሎም የገለልተኛና ነፃ ፍ/ቤቶች፤ የዲሞክራዊ ተቋማት፤ ነፃ ፕሬስ ወዘተ… መኖር ሁሉም በህግ የበላይነት ጽንስ ሀሳብ ውስጥ የሚካተቱ ናቸው። ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ የሊብራል ዲሞክራሲ ጠበል አልተጠመቁም በሚባልላቸው መንግስታት (ለምሳሌ በቻይና) ጽንሰ ሀሳቡ ስልጣን ያለው አካል በሚያወጣቸው ህጐች መሰረት መግዛትና ማስተዳደር ላይ ብቻ የተገደበ ነው።
    የህግ የበላይነት መርህ የአስተዳደር ህግ (በተለይ በእንግሊዝ) የተተከለበት መሰረት ነው። በዚህ መርህ መሰረት ስራ አስፈፃሚው፣ የአስተዳደር መ/ቤቶች እና የአስተዳደር ጉባዔዎች የሚሰጡት ውሳኔ በህጉ መሰረት መሆን ይኖርበታል። በመንግስት አስተዳደር ውስጥ ህጋዊነት የሚሰፍነው ስልጣን የተሰጠው ማናቸውም የመንግስት አካል የሚወስዳቸው እርምጃዎች፣ የሚፈጽማቸው ድርጊቶች፣ የሚሰጣቸው ውሳኔዎች እና የሚያወጣቸው ደንብና መመሪያዎች በህግ ጥላ ስር መሆናቸው ሲረጋገጥ ነው።
    የመንግስት ባለስልጣናት ውሳኔ በህግ ከተቀመጠው የስልጣን ክልል በላይ ከሆነ ውሳኔው የህግ የበላይነት መርህን እንደሚጥስ ጥርጥር የለውም። ህጋዊነት መከበሩን ማረጋገጥ ማለት አስተዳደራዊ ድርጊት፣ ውሳኔ፣ እርምጃ፣ ደንብና መመሪያ በህግ በተቀመጠው የስልጣን ገደብ ውስጥ መሆኑን አሊያም አለመሆኑን ማረጋገጥ ማለት ነው። ይህ ደግሞ የመደበኛ የፍርድ ቤቶች ተግባር ነው። ይህንን ተግባር በሚያሳንስ መልኩ በፍርድ ቤቶች የዳኝነት ስልጣን ላይ በህግ አውጭው የሚደረግ ገደብ በውጤቱ የህግ የበላይነት መርህን ይሸረሽራል። ገደቡ በህግ የበላይነት መርህ ላይ ከሚፈጥረው አደጋ በተጨማሪ የዜጎችን ፍትህ የማግኘት መብት ያጣብባል። በተለይም ይህ መብት ህገ-መንግስታዊ እውቅና የተሰጠው ከሆነ የፍርድ ቤቶችን ስልጣን መገደብ ዞሮ ዞሮ የዜጎችን ህገ-መንገስታዊ መብት መገደብ ነው።
    የህግ የበላይነት መርህ የአስተዳደር ህግ መሰረት ብቻ ሳይሆን ገደብ ጭምር እንደሆነ ማውሳት ያስፈልጋል። የውሳኔን ህጋዊነት ማረጋገጥ በይዘቱ ላይ መቆጠብን ያስከትላል። ፍ/ቤቶች የህግ የበላይነት በማስከበር ሚናቸው የአስተዳደራዊ ውሳኔዎች ይዘት እንዳያጣሩ ወይም በፖሊሲ ጥያቄዎች ጣልቃ እንዳይገቡ ይገድባቸዋል።
    የስልጣን ክፍፍል
    የስልጣን ክፍፍል በአገራችን ህገ መንግስታዊ መርህ ሲሆን ህግ አውጭው፤ ህግ ተርጓሚውና ህግ አስፈፃሚው ያላቸውን ስልጣን ከፋፍሎ ያስቀምጣል። ይሁን እንጂ ከዚህ መርህ በተቃራኒ የአስተዳደር ህግ ከተግባራዊ ምክንያቶች የተነሳ ስራ አስፈፃሚው አካል ሕግ ከማስፈፀም ስልጣኑ በተጨማሪ ህግ የማውጣትና ህግ የመተርጐም ተግባራትን እንዲያከናውን በልዩ ሁኔታ ይፈቅዳል። እነዚህ ተደራራቢ ስልጣናት የመንግስት አስተዳደርን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ በልዩ ሁኔታ የተሰጡ እንጂ በመርህ ደረጃ ከስልጣን ክፍፍል መሰረተ ሀሳብ ጋር ይጋጫሉ። ስለሆነም የህገ መንግስቱ የስልጣን ክፍፍል መርህ የአስተዳደር መስሪያ ቤቶች ደንብና መመሪያ የማውጣት እና ዳኝነታዊ ውሳኔ የመስጠት ስልጣን በአፈፃፀም ረገድ በጠባቡ እንዲተረጐም በማድረግ የዚህ ስልጣናቸው ገደብ ሆኖ ያገለግላል።
    ይኸው መርህ ፍርድ ቤቶች ሚናቸው እስከየት ድረስ እንደሚዘልቅ ይወስናል:: መደበኛ ፍ/ቤት በህግ ተለይተው በታወቁ የምርመራ ምክንያቶች ስልጣን ካልተሰጠው በስተቀር በስልጣን ውስጥ የተፈፀመ ድርጊት ከማረም መቆጠብ ይኖርበታል። ፍ/ቤቶች በስልጣን ውስጥ የተፈፀመ ድርጊትን የሚያርሙ ከሆነ በስራ አስፈፃሚው ስልጣን ጣልቃ በመግባት የስልጣን ክፍፍል መርህን ይጥሳሉ።
    የአስተዳደር ህግ እና የሰብዓዊ መብት አፈፃፀም
    የአስተዳደር ህግ የሰብዓዊ መብትን በማስጠበቅ ረገድ ያለው ሚና የሁለቱን ትስስር በሚገባ ያሳየናል። ህጉ በሰብዓዊ መብት አጠባበቅና አፈፃፀም ላይ ያለውን አዎንታዊ ተፅእኖ በሚገባ ለመረዳት ከሰብዓዊ መብቶች አተገባበር አንፃር የመንግስትን ግዴታ መተንተኑ አግባብነት ይኖረዋል። እነዚህም ሚናዎች (ግዴታዎች) የማክበር (respect) የማስከበር (protect) እንዲሁም የመፈጸምና የማስፈፀም (enforcement) ናቸው።
    በመጀመሪያው መብቶችን የማክበር የመንግስት ሚና ዜጐች ነፃ ሆነው መብታቸውን ሲጠቀሙ ከየትኛውም የመንግስት አካል የሚመጣ ጣልቃ ገብነትን ይገድባል። በተለይም መሰረታዊ በሚባሉት በህይወት የመኖር፣ የመፃፍ፣ የመናገር፤ የፈለጉትን ሀይማኖት የመከተል፤ በነፃነት የመዘዋወርና ንብረት የማፍራት መብቶችና ነፃነቶች በተግባር የሚረጋገጡት መንግስት እጁን ሲሰበስብ ነው። እነዚህ መብቶች በመንግስት በተለይ በስራ አስፈፃሚውና በስሩ ባሉት የአስተዳደር ተቋማት ውሳኔ፤ ትዕዛዝ፤ ደንብና መመሪያ አማካይነት አደጋ ላይ ሊወድቁ ይችላሉ። ህገ መንግስቱ የበላይ ህግ እንደመሆኑ ይህን የሚቃረን ህግ፣ ውሳኔና አሰራር ሁሉ ተፈፃሚነት አይኖረውም። ይህን መሰሉ የህገ መንግስታዊነት ጥያቄ በአስተዳደር ህግ ውስጥ አይወድቅም። ይሁን እንጂ የህገ መንግስታዊነት ብቻ የሚመስል ጥያቄ በአስተዳደር ህግ ማእቀፍ የሚሸፈንበት አጋጣሚ ሰፊ ነው።
    በአንድ የአስተዳደር ተቋም የወጣ መመሪያ በህግ አውጭው ከተሰጠ የውክልና ስልጣን በማለፍ የዜጐችን ሰብዓዊ መብት የሚገድብ ሆኖ ከተገኘ በውስጡ የህገ መንግስታዊነት (constitutionality) ጥያቄ ያዘለ ቢሆንም በዋናነት ግን የአስተዳደር ህግ ሊመልሰው የሚገባ የህጋዊነት (legality) ጥያቄ ነው። ልዩነታቸውን የበለጠ መረዳት እንዲያስችልን የሚከተለውን የድሮው የገቢዎች ሚኒስቴር የአሁኑ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን መመሪያ እንመልከት።
    ማንኛውም የጉምሩክ ፖሊስ ሰላማዊ ስልፍና የስራ ማቆም አድማ ማድረግ አይችልም።
    ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት ለማንኛውም ሰው የተረጋገጠ መብት ነው። መብቱን የሚያጎናጽፈው የአንቀጽ 30 ንዑስ ቁጥር 1 እንዲህ ይነበባል።
    ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን መሳሪያ ሳይዝ በሰላም የመሰብሰብ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት አለው።
    አንድ መመሪያ በስራ አስፈፃሚው አካል ሲወጣ ከህግ አውጭው በግልጽ የተሰጠ የውክልና ስልጣን (Delegation) ሊኖር ይገባል። መመሪያው የውክልና ስልጣኑን ገደብ ካለፈ ከስልጣን በላይ (Ulta vires) ነው። ስለሆነም በህግ ፊት ዋጋ አልባ (null and void) ነው። የገቢዎች ሚኒስቴር ይህን መመሪያ ሲያወጣ የስልጣን ምንጩን የጉምሩክ ባለስልጣንን ለማቋቋምና አስራሩን ለመወሰን የወጣው አዋጅ ቁ. 368/1995 አንቀጽ 8 (2) (ሐ) እንደሆነ ይጠቅሳል። ይህ የተጠቀሰው የህግ ድንጋጌ እንዲህ ይነበባል።
    የጉምሩክ ህግ እንዲያስከብር ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የተመደበን የፖሊስ ኃይል ሚኒስቴሩ የፌደራል ፖሊስ አዋጅን ተከትሎ በሚያወጣው መመሪያ መሰረት በስራ ያሰማራል። ያስተዳድራል። ጥፋት ሲገኝም ያሰናብታል።
    ይህ አንቀጽ የጉምሩክ ፖሊስ ሰላማዊ ሰልፍ እንዳያደርግ በመመሪያ እንዲከለክል ለገቢዎች ሚኒስቴር ስልጣን አይሰጥም። ከተወካዮች ምክር ቤት ግልፅ ስልጣን ባልተሰጠበት ሁኔታ የወጣው ይህ መመሪያ ህጋዊነት ሆነ ተፈፃሚነት የለውም። የአስተዳደር ህግ ይህን መሰል መመሪያዎች በዘፈቀደ እየወጡ የዜጐችን መብትና ነፃነት እንዳይጥሱ በተለያዩ መንገዶች በመቆጣጠር መንግስት ሰብዓዊ መብት የማክበር ግዴታውን እንዲወጣ ያደርጋል።
    የመንግስት የማስፈፀም ኃላፊነት አብዛኛውን ጊዜ ከማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ መብቶች ጋር በቀጥታ ተያይዞ ይነሳል። መንግስት በዜጐች መብት ላይ ጣልቃ አለመግባቱ ወይም እጁን መሰብሰቡ ብቻ አይበቃም። ለዜጋው መሰረታዊ አገልግሎቶችን ማለትም ጤና፣ መብራት፣ ውሃ፣ መንገድ ወዘተ… ካላቀረበ ነፃ መሆን በራሱ ፋይዳ የለውም።
    የአስተዳደር ህግ እና የሰብዓዊ መብት ትሰስር ከመንግስት የማስከበር ግዴታ አንጻርም ሊቃኝ ይችላል። ከዚህ አንጻር መንግስት ሰብዓዊ መብትን በማስከበር ኃላፊነቱ መብት እንዳይጣስ የስልጣን መቆጣጠሪያ ስልቶች በህግ እና በተቋማዊ አደረጃጀት የማጠናከር፣ በመብት መጣስ ጉዳት ለደረሰበት ዜጋ ፈጣን ፍትህ የሚያገኝበትን ስርዓት መዘርጋት አለበት ማለት ነው። በአጭር አገላለጽ ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ መንግስት የዳበረ የአስተዳደር ህግ እና የአስተዳደር ህግ ስርዓት መቅረጽ፣ መትከልና ማጐልበት ይጠበቅበታል።
    መሰረታዊ የመንግስት አስተዳደር መርሆዎች
    መልካም አስተዳደር ምንም እንኳን በጥቅሉ ሲታይ ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ተቋማዊ እንዲሁም የአመራር እና የአሰራር ሂደቶችን የሚመለከቱ ዘርፈ ብዙ እንደምታዎች ያሉት ቢሆንም በህግ ማዕቀፍ ውስጥ ሲታይ ግን ከአስተዳደር ፍትህ ጋር አቻ ሆኖ ሊገለጽ ይችላል። መልካም አስተዳደር ዋና ግቡ ዜጐች ብቁና ውጤታማ አገልግሎት እንዲያገኙ ማስቻል እንዲሁም የሚደርስባቸውን አስተዳደራዊ በደል መቅረፍ እና አስተዳደራዊ ፍትህን እውን ማድረግ እንደመሆኑ ሁለቱን ነጣጥሎ ማየት ያስቸግራል። መልካም አስተዳደር ሆነ የአስተዳደር ህግ በራሳቸው አቅጣጫና ሂደት ተጉዘው የግባቸው መድረሻ የአስተዳደር ፍትህን ማስፈን ነው። ስለሆነም በይዘቱ ሰፊ በሆነ የመልካም አስተዳደር እሳቤ ውስጥ የአስተዳደር ህግ አንድ ቁስ ሆኖ በማገልገል የተቆራኘና የተዛመደ ተግባራዊ እገዛ ያደርጋል።
    በመልካም አስተዳደርና በአስተዳደር ህግ መካከል ያለውን ተዛምዶ በቅጡ ለመቃኘት ህግ በአስተዳደሩ አካሄድ (Administrative behavior) ወይም በስራ አስፈፃሚው እንቅስቃሴ ላይ ምን አይነት አዎንታዊ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል? ለሚለው ጥያቄ በተግባር የታገዘ ጥልቅ ጥናት ምላሽ መስጠት ይጠይቃል። ይሁን እንጂ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ያሉትን ሚናዎችና ተግባራት ቢያንስ እንደጠቅላላ ሀሳብ በመውሰድ የአስተዳደር ህግ እንደ አንድ የህግ ዘርፍ የራሱ አዎንታዊ ፋይዳ እንዳለው መደምደም እንችላለን። ያም ሆኖ ግን አስተዳደሩ መልካም እንዲሆን የአስተዳደር ህግ ስልጣን ከመቆጣጠር ባሻገር እንዴት ተቃኝቶ መቀረጽ አለበት? የሚለው ጥያቄ ለአስተዳደር ህግ አጥኚዎች ሆነ ምሁራን የውይይት ምንጭ ብቻ ሳይሆን የጥናት መሰረት መሆን ያለበት ጉዳይ ነው።
    የመልካም አስተዳደር እና የአስተዳደር ህግን ተዛምዶ ለማየት የሁለቱም መድረሻ ከሆነው የአስተዳደር ፍትህ ትርጓሜ እንነሳለን። የአስተዳደር ፍትህ በህግ ስልጣን የተሰጣቸው የመንግስት አካላት ስልጣናቸውን በሚገለገሉበት ወቅት ከዜጐች መብትና ነፃነት አንጻር ፍትሃዊ መሆን እንዳለባቸው የሚደነግግ መርህ ነው። የመንግስት አስተዳደር ፍትሃዊ ሲሆን መልካም ይሆናል።
    የአስተዳደር ፍትህን በማሳካት ረገድ ሁለት ዓበይት ነጥቦች ቁልፍ ቦታ ይኖራቸዋል። ይኸውም፡-
    አንደኛ፦ የመንግስት ባለስልጣናት ወይም የአስተዳደር መስሪያ ቤቶች ስልጣናቸውን በሚገለገሉበት ወቅት አነስተኛ ለሆኑ የስነ-ስርዓት ደንቦች እና ተቀባይነት ላላቸው መርሆዎች መገዛት አለባቸው። ከአነስተኛ የስነ-ስርዓት ደንቦች በተጨማሪ የመንግስት አስተዳደር ተቀባይነት ባላቸው የህግ፣ የአስተዳደርና የፍትህ መርሆዎች መመራት አለበት።
    ከእነዚህ መካከል በዋናነት የሚከተሉት ይጠቀሳሉ።
    የህጋዊነት መርህ (ህጋዊ ስልጣን ሳይኖር አንዳችም እርምጃ አለመውሰድ፤ በህጉ መሰረት መወሰን)
    የሚዛናዊት መርህ (የአስተዳደር አካላት ውሳኔ ወይም እርምጃ እንደየሁኔታው ብዙ ነገሮች ግምት ያስገባ እንጂ ፍርደገምድል መሆን የለበትም።)
    የተመጣጣኝነት መርህ (የሚወሰደው እርምጃ ተፈጸመ ከተባለው ጥፋት አንፃር ተመጣጣኝ መሆን አለበት።)
    የእኩልነት መርህ (ተመሳሳይ በሆኑ ሁኔታዎች ወይም ጉዳዮች አስተዳደሩ የተለያየ ውሳኔ ላይ መድረስ የለበትም። ተመሳሳይ ሁኔታዎች በተመሳሳይ መንገድ መወሰን አለባቸው።)
    ለውሳኔ በቂ ምክንያት መስጠት (አስተዳደራዊ ውሳኔ የተወሰደበት ምክንያት በግልጽ መጠቀስ አለበት። ውሳኔውም ፈጽሞ የማያሳምንና ኢ- ምክንያታዊ መሆን የለበትም።)
    ሁለተኛ፦ ከላይ የተመለከቱትን ደንቦችና መርሆዎች በመጻረር በህግ ከተወሰነው ስልጣን በላይ እርምጃ ከተወሰደ መብታቸው የተጐዳ ዜጐች አቤቱታ አቅርበው ፍትህ (መፍትሄ) የሚያገኙበት መንገድ መኖር አለበት። በአስተዳደር አካላት መብታቸው የተጣሰ ሰዎች ቀላል በሆነ ስነ-ስርዓት አቤቱታ አቅርበው ቀልጣፋ መፍትሔ የሚያገኙበት አሰራር ወይም መንገድ ከሌለ የአስተዳደር ፍትህ አለ ለማለት አይቻልም። ለምሳሌ አካልን ነፃ የማውጣት መብት በህገ-ወጥ መንገድ ከ48 ሰዓት በላይ የታሰረ ሰው ራሱ በቀጥታ ወይም በሌላ ሶስተኛ ወገን በቀላሉ አቤቱታ አቅርቦ ነፃ የሚለቀቅበት ፈጣን ስነ-ስርዓት ነው። በተመሳሳይ መልኩ በህገ ወጥ መንገድ ንብረቱን በአስተዳደደሩ የተቀማ ወይም ፈቃዱ አለአግባብ የተሰረዘበት ሰው ቀላል በሆነ ስነ-ስርዓት መፍትሔ የሚያገኝበት የህግ ድንጋጌ ሊኖር ይገባል። ለዚህም ነው የአስተዳደር ህግ መኖር ለአስተዳደር ፍትህ ሆነ ለመልካም አስተዳደር ወሳኝ መሳሪያ ነው የሚባለው። የአቤቱታው ስርዓት እንዳለ ሆኖ የአስተዳደራዊ ፍትህ የሚገኝበት ተቋም ገለልተኛ፣ ተደራሽ እና ነፃ ሆኖ ቀልጣፋና ውጤታማ ግልጋሎት መስጠት መቻሉ የአስተዳደር ፍትህን በማሳካት ረገድ ዋናውና መሰረታዊው ቅድመ ሁኔታ ነው።
    ተጠያቂነት ግልፅነት እና የህዝብ ተሳትፎ
    የመልካም አስተዳደር ፅንስ ሃሳብ በቀጥታ ከሚጋራቸው የመንግስት አስተዳደር መርሆዎች መካከል ግልፅነት፣ ተጠያቂነት እና የሕዝብ ተሳትፎ ዋናዎቹ ናቸው። በእነዚህ መርሆዎች ላይ የተተከለ መልካም አስተዳደርን በአንድ አገር ውስጥ በተጨባጭ ለማስፈን ከህግ ማእቀፍ ውጭ የተቋማዊና የአሰራር ለውጦች መዘርጋትና መዳበር ሰፊውን ድርሻ እንደሚይዝ እሙን ነው። ሆኖም የህግ ሚናም መዘንጋት የለበትም። የአስተዳደር ህግ ግልፅነት፣ ተጠያቂነት እና የህዝብ ተሳትፎ በተግባር መፈፀማቸውን በማረጋገጥ ረገድ አንድ ቁልፍ መሳሪያ ነው።
    ግልፅነት በጠቅላላው በመንግስትና በግለሰብ መካከል ያለውን ግልፅ የመረጃ ልውውጥ ያመለክታል። ዜጎች የመንግስት አሰራሮች፣ ዕቅዶች፣ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች፣ አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎችን በተመለከተ በቂ መረጃ ከሌላቸው የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ይሳናቸዋል። የመንግስት ባለስልጣናትም ከተጠያቂነት ያመልጣሉ። የመንግስት ገበና ሳይታወቅ ተጠያቂነት አይታሰብም።
    በህግ ማእቀፍ ውስጥ ስናወራ ግልፅነት የዜጎች መረጃ የማግኘት መብት ነው። የኢ.ፌ.ድ.ሪ ሕገ መንግስት የመንግስት አሰራር ለህዝብ ግልፅ በሆነ መንገድ መከናወን እንዳለበት በመርህ ደረጃ ይደነገጋል። ይህ ህገ- መንግስታዊ መርህ በተግባር የሚረጋገጠው ይህን የሚያስፈፅም ዝርዝር ህግ የወጣ እንደሆነ ነው።
    በአገራችን ዜጎች መረጃ እንዲያገኙ የሚያስችላቸው ስርዓት በ2002 ዓ.ም. በወጣው የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁ. 590/2002 የህግ ማዕቀፍ ተበጅቶተለታል። በተግባር ሲታይ ግን የመንግስት አዋጆች፤ ደንቦችና መመሪያዎች፣ አሰራሮችና ውሳኔዎች ግልፅነት ጉዳይ የሀገሪቱን የህግ ስርዓት ጥላሸት ቀብቶታል። የህጎች ህትመት እና ስርጭቱ አሁንም ድረስ በጣም በመጨረሻው ደረጃ ላይ ይገኛል። ምንም እንኳን አዋጆችና ደንቦች ውጤት የሚኖራቸው በፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትመው ሲወጡ ቢሆንም በስርጭት ችግር የተነሳ ተደራሽ አይደሉም።
    ግልፅነት ብቻውን ተነጥሎ የቆመ መርህ ሳይሆን ተጓዳኝ ከሆነው የሚስጥራዊነት ደንብ ጋር እየተመዘነ እና እየተመዛዘነ መለኪያ ሊበጅለት ይገባል። ግልፅነት ለመንግስት አሰራር እና ለህዝብ ጥቅም ወሳኝ እንደሆነ ሁሉ ከአገር ፀጥታና ደህንነት ብሎም ከዜጎች የግል መብት አንፃር የተወሰኑ መረጃዎች በሚስጥር እንዲጠበቁ ያስፈልጋል። በሚስጥር ሊጠበቁ የሚገባቸው መረጃዎች የመንግስት ባለስልጣናትና ሠራተኛው በኃላፊነቱ ደረጃ ለይቶ እንዲያዛቸው የሚያስችል ሚስጥራዊነታቸውን የመመደብና የመፈረጅ ዘዴና ስርዓት ሊኖር ይገባል።
    የአስተዳደር ህግ የግልፅነት ብቻ ሳይሆን በህገመንግስቱ ላይ የተቀመጠውን የተጠያቂነት መርህ ማስፈጸሚያ መሳሪያ ጭምር ነው። ህጉ የአስተዳደር አካላትና ባለስልጣናት ለድርጊታቸው ተጠያቂ የሚሆኑበትን ስርዓት ከመዘርጋት ባሻገር ጠያቂ የሆኑ አካላትን በመለየት የተቀናጀ የስልጣን መቆጣጠሪያ ስልት ይቀይሳል።
    ዴሞክራሲን እውነተኛ ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ ዜጎች በመንግስት አስተዳደር ውስጥ የነቃ ተሳትፎ ማድረጋቸው ነው። ህገ መንግስቱ ዜጎች የሚያስተዳድሯቸውን በመምረጥ ብቻ ሳይሆን በቀጥተኛ ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ ሉአላዊነታቸው እንደሚረጋገጥ ይደነገጋል።d የሕዝብ ተሳትፎ በተወሰነ መልኩ አስገዳጅ በሆኑ ድንጋጌዎች በተግባር ሊተረጎም ይገባል። በተለይ በአስተዳደር መስሪያ ቤቶች የህግ ማውጣት ሂደት ውስጥ የአስተዳደር ህግ እና የሕዝብ ተሳትፎ ተነጣጥለው ሊታዩ አይችሉም። ውጤታማ የአስተዳደር ህግ ሲኖር በህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጠው ‘ህዝብ በመንግስት አስተዳደር ውስጥ የመሳተፍ’ መብቱ በተጨባጭ ይረጋገጣል።
SURAFEL

This blog is for individuals and private organizations who want to read the FDRE Constitution as well as the interpretations of the Constitution as well as vari